ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ የልማት ተሳትፎን እንድናጎለብት መነሳሳት ፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ የልማት ተሳትፎን እንድናጎለብት መነሳሳት ፈጥሮልናል

ማያ ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ የልማት ተሳትፎን እንድናጎለብት መነሳሳት ፈጥሮልናል ሲሉ የምስራቅ ሐረርጌና የማያ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ነዋሪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁን በማስመልከት ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በማያ ከተማ አካሂደዋል።
በድጋፍ ሰልፉ አመራሮች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ መምሕራንና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ሰልፈኞቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬትንና ልማትን የሚያወሱ የተለያዩ መልዕክቶች በማስተላለፍ ደስታቸውን በሕብረት ገልፀዋል።
ከተሳተፉት መካከል ወጣት ፈቲሕ መሀመድ ፤ የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ መደሰቱን ገልጿል።
የግድቡ መጠናቀቅ ለወደፊቱ መንግስት የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎችን በጋራ ለማከናወን መነሳሳትን ፈጥሮብናል ብሏል።
የሕዳሴ ግድቡ መመረቅ በራስ አቅምና በጋራ መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ያለችው ደግሞ ወጣት እሌኒ አብዱላሂ ናት።
የግድቡ መመረቅ ለቀጣይ የልማት ስራዎች መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ተናግራለች።
ታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ አንድነታችንን ለዓለም የገለጽንበት ትልቁ ተምሳሌታችን ነው ያለው ወጣት አቡሽ መገርሳም በቀጣይም ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመፈጸም ተዘጋጅተናል ብሏል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለኝን በመለገስ ድጋፍ አድርጌያለሁ ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ መገርሳ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅትም ለምረቃ በመብቃቱ ደስታ ተሰምቶኛል፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት የድጋፍ ስራዬን አጠናክራለሁ ብለዋል።
በሐረማያ ከተማ ስታድየም ላይ ለተገኘው ሕዝብ ንግግር ያደረጉት የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢፍራሕ ወዚር (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሕዝቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
ለዚሕም ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ከንቲባዋ፤ በዚሁ መነሳሳት ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብተን ለማጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን መጠቀል አለብን ብለዋል።
ግድቡን መገንባት ኢትዮጵያዊያን ይቻላልን በተግባር ያሳየንበት ነው ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ ናቸው።
ሕዝቡ አሁንም መሰል የልማት ድጋፎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።