በዓላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ መሆን ይቻላል- ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዓላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ መሆን ይቻላል- ተማሪዎች

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ):- በዓላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ መሆን ይቻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ።
ተማሪዎቹ በቀጣይም የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በትጋትና ተጨማሪ ጥረትን በማከል ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከተማሪዎቹ መካከልም የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 560 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ አዲሱ አየለ፤ ውጤቱ ጠንከሮ በመስራቱ፣ የመምህራኑ እና የወላጆቹ እገዛ ታክሎበት ለውጤት መብቃቱን ተናግሯል።
ተማሪ ቃልኪዳን ምትኩም 464 ነጥብ ማምጣቷን ገልጻ ውጤቱን ለማስመዝገብ ጊዜዋን ያለመታከት በንባብ ማሳለፏን ተናግራለች።
በዓላማችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረን ከሰራን፤ የመምህራን እገዛና የወላጆች ክትትል ከታከለበት ከፍተኛ ውጤት ከማምጣት የሚያግድ ነገር አለመኖሩን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ማቱሳላ ጎና፤ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻልና የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ የተለያዩ የማስተማሪያ ስነ ዜዴዎችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዚህም አዳሪ ትምህርት ቤቱ በ2017 ዓ/ም 72 ተማሪዎችን ሀገር አቀፍ ፈተና አስፈትኖ ሁሉም ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የትምህርት ስራ የማይቆራረጥ ዕቅድ፣ ክትትልና ድጋፍ እንደሚፈልግ ጠቁመው በዚህም የተማሪዎች ውጤት በየዓመቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዞኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመረው ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ሳኦል ናቸው።
በዞኑ በየአመቱ መቶ በመቶ ተማሪዎችን የሚያሳልፈውን የሊቃ ትምህርት ቤት ልምድ የማስፋትና ሌሎች ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት አሰጣጡን በማጠናከር፣ ለተማሪዎች የሚደረገውን ድጋፍ በማሻሻልና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን መጠነ ማለፍ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።