ግድቡ ለስኬት በመብቃቱ በትጋት እንድንሰራ መነሳሳትን ፈጥሮልናል- ታዳጊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ግድቡ ለስኬት በመብቃቱ በትጋት እንድንሰራ መነሳሳትን ፈጥሮልናል- ታዳጊዎች

ሰቆጣ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ለስኬት በመብቃቱ በቀጣይ በትጋት እንድንሰራ መነሳሳት ፈጥሮልናል ሲሉ በሰቆጣ ከተማ ታዳጊዎች ገለጹ።
በሕዳሴው ግድብ ግንባታ የተመዘገበው አኩሪ ውጤት በሌላውም ልማት ላይ እንዲደገም የሚደግፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የሕዳሴው ግድብ ስኬት ጠብቀው በማስቀጠል ሌላ ድል እንዲሹ የሚያደርግ በመሆኑ ደስታቸው ወደር እንደሌለውም አንስተዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ታዳጊ ኤልዳና ሃይሉ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት፤
የሕዳሴው ግድብ እውን እንዲሆን በትምሕርት ቤታቸው ገንዘብ ማዋጣታቸውን አውስታለች።
አሁን ላይ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ አደባባይ በመውጣት ከአካባቢ ጓደኞቿ ጋር በመሆን ደስታዋን ለመግለጽ እንዳስቻላት ተናግራለች።
ትውልዱ የሕዳሴውን ግድብ ገንብቶ ለኛ ታዳጊዎች በማስረከበቡ ታላቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብላለች።
ሌላዋ ታዳጊ ፋሲካ አወጣ በበኩሏ፤ የሕዳሴው ግድብ ለስኬት በመብቃቱ እኛ ታዳጊዎች በኩራት ትምህርታችንን በመከታተል በቀጣይ ከዚህ ከፍ ያለ የልማት ሀሳብ ይዘን እንድንሰራ መነሳሳትን ፈጥሮልናል ብላለች።
የሕዳሴው ግድብ የትውልዱ አሻራ በመሆኑ እኛ ታዳጊዎች ታሪኩንና ቅርሱን ጠብቀን በማስቀጠል ሌላ ድል እንድንሻ የሚያደርገን በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ስትል ገልጻለች።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመጪው ትውልድ ጸጋና በረከት መሆኑን ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን የአድዋ ድል በሕዳሴው ግድብ በመድገም ለአዲሱ ትውልድ ማስረከቡ ታላቅ ኩራት መሆኑን አንሰተው፤ አዲሱ ትውልድም ታሪኩን በመጠበቅ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
የሕዳሴው ግድብ የትውልዱ አሻራ ነው፤ ግድቡን በሕብረት እንደገነባነው ሁሉ በቀጣይ በድህነት ላይ በአንድነት መዝመት ይገባናል ብለዋል።
በሰቆጣ ከተማ ትናንት በተካሄደው የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ በርካታ ሕጻናትና ታዳጊዎች መሳተፋቸውም በወቅቱ ተገልጿል።