የሰላምና የፍቅር መገለጫ የሆነው የጊፋታ በዓል ሲከበር አብሮነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምና የፍቅር መገለጫ የሆነው የጊፋታ በዓል ሲከበር አብሮነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ሊሆን ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ የሰላምና የፍቅር መገለጫ የሆነው የወላይታ የዘመን መለወጫ(ጊፋታ) በዓል ሲከበር አብሮነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ሊሆን እንደሚገባ የወላይታ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የዘንድሮ የጊፋታ በዓልን በማስመልከት '' ጊፋታ ለህብረብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ፤ የወላይታ የዘመን መለወጫ(ጊፋታ) የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በዓሉ ሲከበር አብሮነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዓሉን በምርምር አጎልብቶ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሸጋገር እየተሰራ መሆኑን አንስተው በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በቅርስነት ለማስመዝገብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም፤ በበኩላቸው የጊፋታን ዕሴቶች በማስተዋወቅ የከተማውን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዛሬው ስፖርታዊ ውድድርም በዓሉን ከማሰብ ባለፈ ስፖርተኞችን የማፍራት አላማ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሂዶ በወንዶችና በሴቶች ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ለወጡ የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።