ቀጥታ፡

የአባይ የቁጭት ጊዜ አብቅቶ የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ መቻል ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ነው

ነገሌ ቦረና፣ ጅማ፣ መቱ ፤ መስከረም 7/ 2018  (ኢዜአ)፡- የአባይ የቁጭት ጊዜ አብቅቶ የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ መቻል ትልቅ ሀገራዊ ስኬት መሆኑ ተገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄደዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ህዝቡ ከማለዳው ጀምሮ የተለያዩ መልእክቶችን የያዙ ባነሮችንና መፈክሮችን በመያዝ ደስታውን ገልጿል።

ሰላማዊ ሰልፉ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል በነገሌ ቦረና፣ በጅማ እና መቱ ከተሞች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየአደባባዮች በመውጣት ድጋፋቸውን በማሳየት ደስታቸውንም አስተጋብተዋል። 

በነገሌ ቦረና ከተማ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት መካከል አቶ እስራኤል ዱባ፣ ሀጂ አወል ሁሴን እና አቶ ሚሊዮን አንዳርጌ፤ በትብብራችን ለስኬት በመብቃታችን ደስታችንን ለመግለጽ ወጥተናል ብለዋል።

የአባይ የቁጭት ጊዜ አብቅቶ የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ መቻል ለሀገራችን ትልቅ ስኬት በመሆኑም ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ ተናግረዋል።

የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን፤ የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ በድህነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ በማሸነፍ እድገትና ማንሰራራትን እውን ለማድረግ ጠንካራ መሰረት መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን አንስተዋል።

የነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሊቻ ዲቃ፤ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ስኬት የዘመናት ቁጭት ያበቃበት፤ ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረት እየተሳካ መምጣቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍም የከተማውና የዞኑ ነዋሪዎች ከማለዳው ጀምሮ በመውጣት ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ከድጋፍ ሰልፉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ሳቢር አባዝናብ እና ወይዘሮ ሹኩሪ አባወሊ፤ በብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ የተገነባው ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ ተደስተናል ብለዋል። 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት ጽናትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በተግባር የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር፤  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የቁጭት ጊዜ አብቅቶ የስኬትና ማንሰራራት ጊዜ ላይ መድረሳችንን ያሳየ ነው ብለዋል።

በመቱ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተገኙት ነዋሪዎች መካከል አቶ ተሰማ አበበ እና አቶ አድማሱ ከበደ፤ በግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በጋራ ደስታችንን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ወጥተናል ብለዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ፤ የግድቡ ግንባታ የሀገርን ሃብት በጋራ በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተግባር ያረጋግጥንበት ነው ሲሉ ተናዋል።

ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም ከቻልን የማናልፈው ችግር የማናሳካው የልማት እቅድ እንደማይኖርም ማረጋገጫ ስለመሆኑ አንስተዋል። 

የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ኤጄርሶ፤ በበኩላቸው በሕዳሴ ግድብ የታየው ህብረ ብሄራዊ አንድነትና የልማት ስኬት በሌሎችም እንዲቀጥል በጋራ መትጋት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም