ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የግብርና ልማት ስትራቴጂ የሰብል ምርታማነትን በማሻሻል ያስመዘገበው ለውጥ አድናቆት የሚቸረው ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የግብርና ልማት ስትራቴጂ የሰብል ምርታማነትን በማሻሻል ያስመዘገበው ለውጥ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን የጀርመን ጊሰን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ኤሚሊ ፖፐንቦርግ ገለጹ።

የጀርመን ጊሰን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ኤሚሊ ፖፐንቦርግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ የግብርና ስትራቴጂዎች ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም የፈጠሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ አምስት ሀገራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተቀረጸው የ "መግፋትና መሳብ" (የፑሽ-ፑል) ፕሮጀክት ላይ መስራታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተተገበረውና የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የአፈር ለምነትና ተባይን የሚከላከለው ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የግብርና ሥነ-ምህዳሩን ማሳደግ የሚያስችሉ ጠንካራ ፖሊሲዎችን መቅረጿ አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በዋናነት የግብርና ሥነ-ምህዳርን ምቹ ከማድረግ ባለፈ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ አሰራሮች በስፋት ተግባር ላይ መዋላቸውን መመልከት መቻላቸውን አንስተዋል።

የሰብል ምርትን ለማሳደግ አንድ መፍትሔ ብቻ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ይልቁንም የግብርና ሥነ-ምህዳር ስትራቴጂዎች እንደሚያስፈልጉና ኢትዮጵያም በዚህ ውጤታማ ስራዎች እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይ በኢትዮጵያ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተተገበሩ ያሉ ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በመኸር፣ በመስኖና በበልግ ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተግባራዊ ያደረገቻቸው ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ፣ በአዝርዕት ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን ለማጥፋት እና በስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን አረም ለመከላከል  ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

"መግፋትና መሳብ" የተሰኘው ቴክኖሎጂ በቆሎና ማሽላን ጨምሮ የተለያዩ ዕጽዋት ዓይነት በአንድ ቦታ በመዝራትና በመትከል   በማሳ ላይ ሊከሰት የሚችልን በሽታን፣ አረምን እና ተባይን በተፈጥሯዊ መንገድ በመከላከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም