ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን የመቻል አቅም ማሳያ ነው

አሶሳ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን የመቻል አቅም ማሳያ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ እና ሌሎች ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በአሶሳ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት የግድቡ በስኬት መጠናቀቅ የመቻላችን ህያው ማሳያ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የአሶሳ ከተማ ነዋሪው እንድሪስ አህመድ እንደተናገሩት፤ ግድቡ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ በመጠናቀቁ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸዋል።

የግድቡ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልፀው እሳቸውም ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በንግድ ስራ የተሰማሩት እንድሪስ የንግዱ ማህበረሰብን በማስተባበር ለግድቡ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በማድረግ በኩል ሲሳተፉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ቀሲስ አበበ ገብረኪዳን በበኩላቸው፤ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ትብብር በሌሎች ትልልቅ የልማት ስራዎች ላይም መድገም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ለማንሰራራት በምታደርገው ጉዞ የሕዳሴው ግድብ ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በህብረተሰቡ ቁጭት እና ተነሳሽነት የተከናወነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ አበበ ብርሃኑ ናቸው።

ግድቡ እውን እንዲሆን የተከፈለው መስዋዕትነት ፍሬያማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባና የመፈጸም አቅማችን የታየበት ነው ብለዋል።

የግድቡ በስኬት መጠናቀቅን አስመልክቶ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በድጋሚ አንድነታችንን የምናሳይበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም