ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሕብረት የመቻል እና የአንድነታችን ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሕብረት የመቻል እና የአንድነታችን ማሳያ ነው
ሮቤ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሕብረት የመቻል እና የአንድነታችን ማሳያ ነው ሲሉ በባሌ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
የግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ከሮቤ ከተማና የባሌ ዞን ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የድጋፍ ሰልፍ በሮቤ ከተማ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና የሮቤ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ነዋሪዎች በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳና ላይ ትዕይንተ ህዝብ ካደረጉ በኋላ በመደ ወላቡ ስታዲየም የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ መኮ ሀጅ አደም፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን አኩሪ ስኬት በሌሎችም የልማት ፐሮጀክቶች ላይ ለመድገም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግራ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት በማጠናቀቋ ኩራት እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ አባገዳ መሐመድሁሴን ቡዴ ናቸው።
ይሔን ስኬት ከመዘከር ባለፈ ሌሎች የልማት ውጥኖችንም ከፍጻሜ ለማድረስ ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረው የግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሕብረት የመቻል እና የአንድነታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግድብ ባሻገር የሀገር አንድነትንና አኩሪ ውጤት ማሳያ ምልክታችን ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የይቻላልን መንፈስ ዳግም ያሳየችበት ታሪካዊ ስኬት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልዪ ናቸው።
የዞኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በሕዳሴ ግድብ ያሳዩትን አንድነት በማጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የመስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሮባ ቱርቼ፤ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሀገር አንድነት ምልክትና ማሳያ ነው ብለዋል።
በግድቡ መጠናቀቅ የተገኘውን ስኬት በሌሎች የልማት ስራዎችም ለመድገም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።