የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ መስከረም 7 /2018 (ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ በተለይም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ገለፃ አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው በክልሉ በተለይም የግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፉን አሰናስሎ በማልማት የወልና የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ በሁሉም ዘርፎች እምቅ አቅሞች መኖራቸውን ገልጸው በተቀናጀ ልማት ጥቅም ላይ በማዋል የጋራ እድገትና ብልጽግናን እውን የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በክልሉ የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋት ምርታማነትን በማሳደግ ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ አሰራሮችን በመከተል እንዲሁም የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም ኢንሼቲቮች ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ ልማት ለማንሰራራት በጋራ መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክልሉ በከተሞችና በገጠር ጭምር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ "የቤተሰብ ብልጽግና" የሚል “ማቴቴ ጅሬኛ” የተሰኘ ስልት ተነድፎ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው ውጤትም እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማትና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከራስ ፍጆታ አልፎ ገቢን በማሳደግ ከቤተሰብም ያለፈ ብልጽግናን እውን የማድረግ ጥረት ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በክልሉ ከኢንዱስትሪ እና የግብርና ልማትም ባለፈ በቱሪዝም፣ አይ ሲቲ እና የማእድን ሃብት ልማት በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።