ቀጥታ፡

ሕዝቡን በማስተባበር በሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ስኬት በሌሎች የሰላምና የልማት ስራዎች ለመድገም እንረባረባለን - አቶ አወሉ አብዲ

አሰላ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ ሕዝቡን በማስተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ስኬት በሌሎች የክልሉ ሰላምና የልማት ስራዎች ላይ ለመድገም እንረባረባለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ተናገሩ።

"በአንድነት አሳክተናል" በሚል መሪ ሃሳብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።


 

በአሰላ ከተማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

አቶ አወሉ አብዲ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ስኬት ቦንድ እና ሌሎች ስጦታዎችን በመለገስ ያላሰለሰ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም የክልሉን ሕዝብ በማስተባበር በሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ስኬት በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በተለይም በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሰላማዊ መንገድ ወደ ሰላም የሚመጡ አካላትን ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የክልሉ መንግስት ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ትኩረቱን የልማት ስራ ላይ እንዲያደርግ የሰላም መንገድ ያልተቀበሉ አካላት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የክልሉ መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትም የምርት አቅርቦትን ከማስፋት ጎን ለጎን ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ያጠናክራል ብለዋል።

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስፋት ስራ በትኩረት እንደሚሰራም አቶ አወሉ አብዲ አስታውቀዋል።

በክልሉ በአምስት ከተሞች የተጀመረውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የማድረስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም