ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን ያሳካነውና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን ያሳካነውና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን ያሳካነውና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ያሳየ ነው ሲሉ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ።
"በአንድነት አሳክተናል" በሚል መሪ ሀሳብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀዳሲንቄዎች እና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ከቢሾፍቱ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተለያዩ መልዕክቶችን በመያዝ በኅብረ ዜማ ታጅበው ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን ያሳካነውና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ያሳየ ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያውያንን አንገት ቀና ያደረገ እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ በርካታ ችግሮችን ተሻግሮ በኢትዮጵያውያን ትብብር የተሳካበትና ለቀጣይ ፕሮጀክቶች መሰረት የጣለ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆምን ሌሎችም በርካታ ፕሮጀክቶችን በመስራት ከድህነት መውጣት እንደምንችል አሳይተናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።