ቀጥታ፡

ኢጋድና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በስደተኞች ጥበቃ ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በስደተኞች ጥበቃ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ ።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በመወከል የተቋሙ የአስተዳደር እና ፋይናንስ ዳይሬክተር ጆሴፓት ኦንያሪ እና የማህበራዊና የጤና ልማት ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሳ አሊ ሜይጌጅ ከኮሚሽኑ የምስራቅ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና ታላላቅ ሐይቆች ቀጣና (ግሬት ሌክስ) ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማማዱ ዲያን ባልዴ ጋር ዛሬ በጅቡቲ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በኢጋድ ቀጣና ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ለግዳጅ ፍልሰት ፈተናዎች ምላሽ መስጠት፣ አሳታፊነትን ለማረጋገጥ እና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

ሁለቱ ወገኖች በስደተኞች ጥበቃ እና በዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ላይ ጠንካራ መፍትሄ ለማበጀት የጋራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

ተቋማቱ በኢጋድ አባል ሀገራት ለሚገኙ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች መረጋጋትን ማስፈን፣ አቅም መገንባት እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመስጠት እንደሚሰሩ ማመልከታቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬታሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም