በሞተር የሚሰሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ የረጅም ዓመታት ጥያቄ የመለሰ ነው - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሞተር የሚሰሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ የረጅም ዓመታት ጥያቄ የመለሰ ነው - ቢሮው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፡- በሞተር የሚሠሩ ጀልባዎች ለአንድ ዓመት ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረን ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር ባሳለፍነው ቅዳሜ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ እንዳሉት፤ ውሳኔው የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ በማነቃቃት የጎብኚዎችን የመጓጓዣ አማራጭ በማስፋት የጉብኝት ሁኔታን ምቹ ያደርጋል።
በአስጎብኚ ድርጅቶችና በባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ በተሰማሩ አካላት በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ መሆኑን አውስተው፤ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ጥያቄውን የመለሰ እና ቱሪዝሙን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተለያዩ ሐይቆች መኖራቸውን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ ከባሕርዳር ጎርጎራ ብሎም የጣና ደሴት ገዳማትን ለማስጎብኘት ውሳኔው የጎላ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
ውሳኔው በቀጣይ በሎጎ እና ዘንገና ሐይቆች የባሕር መጓጓዣ እንዲኖር የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ያግዛል ነው ያሉት።
በቱሪዝም ዘርፉ ቁልፍ የሆነው ምቹ እና አማራጭ ትራንስፖርት መኖር የጎብኚዎችን ቁጥር እንደሚጨምር አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ከመጣው የውኃ ቱሪዝም በስፋት ተጠቃሚ ለመሆንና አሁን ያሉትን ውስን የባሕር መጓጓዣዎች ቁጥር በማሳደግ ረገድም ሁነኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።
ባለሀብቶችም መንግሥት የሰጠውን ለአንድ ዓመት የሚቆይ ትልቅ ዕድል ባለማሳለፍ ራሳቸውን እና ሀገርን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።
መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማንኛውም በንግድ ሥራ የተሠማራ ሰው፤ ፈጣን እና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓሣ ማጥመጃና ለአጫጭር ርቀት የመንገደኛ ማጓጓዣ የሚውሉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች፣ በመካከለኛ ሐይቆች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፤ ለቱሪስት እና ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ፈጣን ጀልባዎች፣ ለቱሪስቶች ጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ግልጽ ወይም በከፊል የተሸፈኑ ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ማስገባት እንደሚቻል ገንዘብ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም ለሰዎች ማጓጓዣ የሚውሉ፣ ለጥናት እና ምርምር የሚያገለግሎ፣ ለግል አገልግሎት የሚውሉ፣ በጸሐይ ኃይል እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ፣ ጠፍጣፋ እና ባለ ጣሪያ የሞተር ጀልባዎች እና የመሳሰሉት ለኢትዮጵያ ሐይቆች ተስማሚ የሆኑ የሞተር ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ማስገባት እንደሚቻልም እንዲሁ።