ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት ዛሬ ላይ ሆኖ የተሻለ ነገን የሚያይና የሚገነባ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት ዛሬ ላይ ሆኖ የተሻለ ነገን የሚያይና የሚገነባ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር እሳቤ የጻፉት 4ኛው መጽሃፍ ''የመደመር መንግሥት'' ዛሬ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።

በመርሃ ግብሩም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መጽሃፉ ''መነሻ''፣ ''መዳረሻ''፣ ''መንገድ'' እና ''መንግስት'' በተሰኙ አራት ሃሳቦች ዙሪያ እንደሚያጠነጥን አብራርተዋል።

በዚህም መጽሃፉ ኢትዮጵያ ለምን ደሃ ሆነች ከሚል ቁጭት እንደሚነሳና የጠራ መፍትሄ እንደሚያመላክት ጠቁመዋል።


 

መፍትሄዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያን መዳረሻ በግልጽ የሚያስቀምጡ መሆኑን አንስተው፣ የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚመኝ ብቻ ሳይሆን እንዲሳካ የሚሰራ ነው ብለዋል።

ሁለንተናዊ እሳቤውም ሌሎችን ለመምሰል የምትጥር ሳይሆን ራሷ ምሳሌ የምትሆን ሀገር ለመገንባት መስራት ነው፣ ይህም በተሳካ ሁኔታ ይከናወናል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ በበርካታ መስኮች የተመዘገበው ስኬትም በዚህ ረገድ አብነት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ኢትዮጵያ እንደምትችል አሳይቷል ብለዋል።

የተሻለችና የበለጸገች ሀገር እውን ለማድረግ መንገዱ ምን ይሁን የሚለው ደግሞ መጽሃፉ የሚያጠነጥንበት ሶስተኛው ሃሳብ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ራዕያችንን ለማሳካት የምንጓዘው መንገድ አካታችና ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ መሆን አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ አካታች ስርዓት መገንባት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ የምንደመረው በአንድ ጭንቅላት ለማሰብ ሳይሆን ስለ አንድ ሀገር በጋራ ለመስራት ነው' ብለዋል።


 

ከዚህ አኳያ መደመር ለኢትዮጵያ የዘመናት ስብራት ፍቱን መድሃኒት መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በሌላ በኩል ለነገ አሻግረን የያዝነው ራዕይ እውን የሚሆነው ጠንካራ መንግስት ሲኖር ነው፣ መንግስት ደግሞ የሁሉም ስኬት መሰረት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የመደመር መንግስት ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን የሚያይና የሚሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም