ኢትዮጵያ በወርቅ የደመቀችበት የኦሬገኑ ታሪካዊ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲታወስ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በወርቅ የደመቀችበት የኦሬገኑ ታሪካዊ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲታወስ

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ አሃዱ ተብሎ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ የቶኪዮውን ጨምሮ በ20ውም ውድድር ላይ ተሳትፎ አደርጋለች።
ኢትዮጵያ ከሻምፒዮናው ተሳትፎ ታሪኮቿ መካከል ከፍተኛ ስኬት ያገኘችበት እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኦሬገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሊቲክስ ሻምፒዮና ነበር።
ዓለም እ.አ.አ. በ2022 ዓለም ከኮቪድ ወረርሽኝ አገግማ በተካሄደው በዚህ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ስኬታማውን የዓለም ሻምፒዮና ያገኘበት ውጤት አስመዘግቧል።
በሻምፒዮናው አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች፣ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ5ሺህ ሜትር ሴቶች፣ አትሌት ጎይቲቶም ገብረስላሴ በሴቶች ማራቶን እና አትሌት ታምራት ቶላ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ኢትዮጵያን አኩርተዋል።
አትሌት ጉዳፍ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ በማግኘት በሻምፒዮናው ሁለት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን በሁለቱም ጾታ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉ ሲሆን አትሌት ለተሰንበት በ10 ሺህ ሜትር የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች።
በተጨማሪም ሞስነት ገረመው በማራቶን የብር፣ ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር ወንዶች መሰናክል ብር፣ ወርቅውሃ ጌታቸው በ3000 ሜትር ሴቶች መሰናክል የብር፣ መቅደስ አበበ በ3000 ሜትር ሴቶች መሰናክል የነሐስ እና ዳዊት ስዩም በ5000 ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ በኦሬገኑ ዓለም ሻምፒዮን ከአራቱ ወርቅ በተጨማሪ አራት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠናቃለች።
የኦሬገኑ ውድድር ኢትዮጵያ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችበት ውድድርም ሆኖ አልፏል።
የዓለም አትሌቲክስ የኢትዮጵያን ስኬት እጅግ አስገራሚ ነው ሲል አድናቆቱን ችሯል።
ደማቅ ስኬት ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ቡድን በአዲስ አበባ ደማቅ የጀግና አቀባበል የተደረገለት ሲሆን አትሌቶቹ በመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች በመዘዋወር ከሕዝቡ ደስታውን በመግለጽ ድላቸውን አክብረዋል።