ቀጥታ፡

የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ያነቃቃል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፡- የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ በሞተር የሚሠሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር እንዲገቡ መወሰኑ የቱሪዝሙን ዘርፍ ይበልጥ ያነቃቃል አለ።

እንደ ሀገር በውኃ ላይ ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ፀጋ መኖሩን የቢሮው ምክትል እና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አበበ ማሪሞ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህ ፀጋ ለመጠቀም ብሎም በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን መንግሥት ሰሞኑን የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ ያሳለፈው ውሳኔ የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም ውሳኔው በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለብቶችን እና ዘርፉን በይበልጥ ያነቃቃል ነው ያሉት።

በሀገር ውስጥ ከሚመረቱት በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡትን በጠቀም በዘመናዊነት፣ በላቀ ምቾት፣ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ ብለዋል።

አሁን ላይ ሐዋሳ ሐይቅ የጀልባ ላይ ጉብኝት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የግዳቦ ግድብ እና ዓባያ ሐይቆችን ወደ ቱሪዝም ገበያ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አንድ ደረጃ ከፍ እንደመሚያደርግ ተናግረዋል።

ለመግዛት አስበው በታክስና ቀረጥ ክፍያ ስጋት ለዘገዩ አካላትም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፣ ጀልባዎችን በማስገባት ለቱሪዝሙ ዘርፉ እድገት እና የላቀ አገልግሎት ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ መክረዋል።


 

መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማንኛውም በንግድ ሥራ የተሠማራ ሰው፤ ፈጣን እና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓሣ ማጥመጃ እና ለአጫጭር ርቀት የመንገደኛ ማጓጓዣ የሚውሉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች፣ በመካከለኛ ሐይቆች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፤ ለቱሪስት እና ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ፈጣን ጀልባዎች፣ ለቱሪስቶች ጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ግልጽ ወይም በከፊል የተሸፈኑ ጀልባዎች፣ ለሰዎች ማጓጓዣ የሚውሉ ጀልባዎች፣ ለጥናት እና ምርምር የሚያገለግሎ ጀልባዎች፣ ለግል አገልግሎት የሚውሉ ጀልባዎች፣ በጸሐይ ኃይል እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ጀልባዎች፣ ጠፍጣፋ እና ባለ ጣሪያ የሞተር ጀልባዎች እና የመሳሰሉት ለኢትዮጵያ ሐይቆች ተስማሚ የሆኑ የሞተር ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ማስገባት እንደሚችል ገንዘብ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም