ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ትብብር በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ መነሳሳትን ፈጥሯል

ሮቤ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታያው ትብብር በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በአንድነት ለመሳተፍ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።

በባሌ ዞን ለታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት እውቅና መርሐ ግብርና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ እውቅና ከተሰጣቸው የንግዱ ማሕበረሰብ አካላት መካከል ሐጅ መሐመድ በየና እንዳሉት፤ ለታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አንድ ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዢ ድጋፍ አድርገዋል።

ግድቡ ብዙ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ለምረቃ በመብቃቱ ቀጣይ በሚከናወኑ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በአንድነት ለመሳተፍ ይበልጥ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ የንብግዱ ማህበረሰብ አካላት መካከል ለሕዳሴው ግድብ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት በመድረኩ እውቅና ያገኙት ሐጅ አብዱልጀባር ሁሴን ናቸው።


 

የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ለትውልድ የሚሻገር አኩሪ ታሪክ እንደምንሰራ በተግባር ያሳየ ውጤት ነው ብለዋል።


 

በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት አንድ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ በመፈፀም እውቅና እንዳገኙ በመጥቀስ አስተያየት የሰጡት ደግሞ ሐጅ ከድር ሐጅ አብዱላሂ ናቸው።

በቀጣይ በሚካሄዱ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።


 

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሀኪም አልይ፤ የዞኑ ማሕበረሰብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ድጋፍ በማድረግ የራሱን አሻራ ማኖሩን ተናግረዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሀብቶቻችን የመጠቀም መብታችንን በተግባር ከማሳየት ባሻገር በቀጣይ በሕዝብ ትብብር ሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳያ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ነገ በሮቤ ከተማ እንደሚካሄድ በመርሐሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም