ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስኬት የአንድነታችን አኩሪ ውጤት ማሳያ ምልክታችን ነው

ዲላ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በሕብረት የመቻል እና የአንድነታችን አኩሪ ውጤት ማሳያ  ምልክታችን ነው ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ ።

የግድቡ ግንባታ በስኬት  መጠናቀቁን አስመልክቶ የፓናል ዉይይት በክልሉ ዲላ ከተማ ፤ የድጋፍ ሰልፍ ደግሞ  በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች  ዛሬ ተካሄዷል።


 

በፓናል ውይይቱ ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ አለሙ(ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ግድቡ የሃገር አንድነትና ኩራት ማሳያ ምልክታችን  ነው፤  ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ የጋራ ትብብር  እንደምትችል ለዓለም አሳይታለችም ብለዋል።

ይሕም ያለንን አቅም በመጠቀም የመልማትና ካደጉት ሀገራት ተርታ የመሰለፍ ሕልማችንን እውን የምናደርግበትና የማንሰራራት ጊዜ መድረሱን ያመላክታል ሲሉ አብራርተዋል ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት በሕብረት የመቻል ምልክት ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ናቸው። 

ግድቡ የኃይል አቅርቦት ሽፋንን በማሻሻል የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ በማፋጠን የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ፤ ግድቡ በኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት  አኩሪ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ እንደ ሃገር የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅም በሕዳሴው ግድብ የታየው አንድነት መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው ፤ ለዚሕም የከተማውን  ሕዝብ  በማስተባበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በይርጋጨፌ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ እመቤት ሃይሉና አቶ ዳዊት ቡኔ ፤  የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል።

ይህንን አኩሪ ስኬት   በሌሎችም የልማት ፐሮጀክቶች ላይ ለመድገፍ  ተሳትፏቸውን  እንደሚያጠናክሩ አስታወቀዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው፤  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  ከግድብም ባሻገር የሀገርን አንድነትንና አኩሪ ውጤት ማሳያ ምልክታችን ነው ብለዋል።

 በወናጎ ወረዳ በተካሄደው ሰልፍ ከተሳተፉት ውስጥ  አቶ ኢዮብ ጎሌ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ተሻግራ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት   በማጠናቀቋ  ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ይሕን ስኬት  ከመዘከር ባለፈ  ሌሎች የልማት ውጥኖችንም ከፍጻሜ ለማድረስ ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በዲላና በዞኑ በየደረጃው በተከናወነው መረሃ ግበር ላይ  አመራሮች፣ ምሁራን፣ የፀጥታ አካላት፣  አባ ገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ  ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም