ቀጥታ፡

ሥልጠናው በፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፦ የብሉምበርግ ሚዲያ ኢኒሼቲቭ ሥልጠና በፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች በብዛት ለማፍራት እንደሚያግዝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።

ብሉምበርግ ሚዲያ ኤኒሼቲቭ አፍሪካ የፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።


 

ሥልጠናው የፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት የአዘጋገብ ክፍተትን ለመሙላትና ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ የምታደርገውን ጉዞ ማሳለጥ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን አንስተዋል።

ይህ ማሻሻያ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ ማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋት፣ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ፣ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ እና የብድር ስጋቶችን በመቀነስ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

እነዚህ ወሳኝ ሀገራዊ ግቦችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ፣ ትብብር እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት በፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት ክህሎቱ የዳበረ ባለሙያ ሚና ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ስልጠናው በኢትዮጵያ የገበያ እድገቶችን የሚዘግቡ እና ለዜጎች በፋይናንስ ዘርፍ ትክክለኛና ታማኝ መረጃ የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን በብዛት ለማፍራት ያስችላል ነው ያሉት።


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሸኔ በበኩላቸው ስልጠናው በኢትዮጵያ ያለው የጋዜጠኝነት ምህዳርን ያስፋዋል ብለዋል።

ጋዜጠኞች በፋይናንሺያል ዘገባ ተጨባጭና ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ በማድረስ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር ያስችላል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን(ዶ/ር) ስልጠናው ለኢትዮጵያ የፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት መጎልበት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዘገባ ለመስራት እንደሚያግዝ አንስተው ይህም የሀገር ግንባታ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ስልጠናው ጋዜጠኛች በፋይናንሺያል ዘርፍ ያላቸውን እውቀት በማዳበር ተጨባጭ መረጃ እንዲያደርሱ ያግዝል ሲሉ ገልጸዋል።


 

ስልጠናው ጋዜጠኞች በእውቅት ላይ የተመሰረት መረጃ ለማህበረሰቡ እንዲያደርሱ ያግዛል ያሉት ደግሞ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አረጋ ይርዳው(ዶ/ር) ናቸው።

ብሉምበርግ ሚዲያ ኤኒሼቲቭ አፍሪካ የፋይናንሺያል ጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዙር ሥልጠና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም