ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቁ በሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ለምናደርገው ተሳትፎ መነሳሳትን ፈጥሮልናል - የንግዱ ማህበረሰብ

ምስራቅ ሐረርጌ፤  መስከረም 6/2018 (ኢዜአ) ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ለምናደርገው ተሳትፎ መነሳሳትን ፈጥሮልናል ሲሉ  በምስራቅ ሐረርጌ ዞን  ለግድቡ ድጋፍ ያደረጉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ። 

በዞኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ እውቅና ከተሰጣቸው የንግዱ ማህበረሰብ አካላት መካከል አቶ መሀመድ ዳውድ እንዳሉት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለት ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፍ አድርገዋል።


 

ግድቡ ለምረቃ በመብቃቱ ልዩ ደሰታ እንደፈጠረላቸው የጠቆሙት አቶ መሀመድ፤ በተለይም የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ለሌሎች የልማት ስራዎች መነሳሳት ፈጥሮልኛል ብለዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አባቷ ላደረጉት ድጋፍ እውቅናን የተቀበለችው ወጣት ሸብሪካ ሼህሻሚል በበኩሏ በግድቡ መጠናቀቅ  መደሰቷን  ስትገልጽ  እርሷም የአባቷን ፈለግ በመከተል ለአገር የሚጠበቅባትን ለመወጣት  መነሳሳቷን  ተናግራለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አብሮነትንና አንድነትን ያሳየንበት የስኬት መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ በንግድ ስራ የተሰማሩት  ወይዘሮ አስማ ስዩም ናቸው


 

ለዚህም ለግድቡ ግንባታ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በህዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላደረጉት  አስተዋጽኦ ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋና አቅርበው በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ያሳዩትን ተነሳሽነት በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ  እንደሚያጠናክሩም ወይዘሮ አስማ አስረድተዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ በወቅቱ እንደተናገሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የዞኑ ህዝብ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡


 

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በትብብር ከተጓዝን የማናሳካው ስራ እንደሌለ ያሳየና  በራስ አቅም መፈጸም እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት  ነውም ብለዋል።

በመርሃ ግብሩም በዞኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ ታላቅ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ በነገው እለት በማያ ከተማ  አስተዳደር ይካሄዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም