ቀጥታ፡

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6 /2018 (ኢዜአ)፦ የ2025/26 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል።

አትሌቲኮ ቢልባኦ ከአርሰናል እና ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከዩኒየን ሴይንት ጊሎስ ጋር በተመሳሰይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ45 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የ15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ ከማርሴይ፣ ጁቬንቱስ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቪያሪያል እና ቤኔፊካ ከካራባግ በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የሻምፒዮንስ ሊጉ የመክፈቻ መርሃ ግብር እስከ መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በ4 ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ከባለፈው የውድድር ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በዚሁ መሰረት 36ቱ ቡድኖች በ4 ቋቶች የተደለደሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ቋት 9 ክለቦች ይገኛሉ።

አንድ ክለብ በራሱ ቋት ካለ ሁለት ቡድንና በእያንዳንዱ ቋት ካሉ ሁለት ክለቦች ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

ይህም አንድ ክለብ ከዚህ በፊት በነበረው የውድድር ፎርማት የሚያደርገውን ስድስት ጨዋታ ወደ ስምንት ከፍ አድርጎታል።

ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባሉ።

ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው ወደ 16ቱ ያልፋሉ።

ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።

ከዚህ ቀደም በውድድሩ ላይ ይሳተፉ የነበሩ 32 ክለቦች በአሁኑ የውድድር አሰራር ወደ 36 ከፍ ማለታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም