በአፋር ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጋራ ተግባቦት ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጋራ ተግባቦት ተፈጥሯል

ሰመራ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጋራ ተግባቦት በባለድርሻ አካላት መካከል መፈጠሩ ተገልጿል።
በክልሉ ሰመራ ከተማ የሴቶችና ህጻናት ጥቃት ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በጋራ ተግባቦቱም ባለድርሻ አካላት፤ የሴቶችና ህፃናትን ጉዳዮች የስራቸው አካል አድርገው እንዲሰሩና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር መሆኑም ተመላክቷል።
በዕለቱ የተገኙት በፍትህ ሚኒስቴር የሴቶች ህፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዳግማዊት አላምነህ እንደተናገሩት መንግስት የህብረተሰቡን ፍትህ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።
እንደ ጠለፋ፣ ጉልበት ብዝበዛ፣ ህገ-ወጥ ዝውውር፤ ትምህርት ያለማግኘትና የመሳሰሉ በህፃናት ላይ የሚደርሱ ወንጀሎችና የመብት ጥሰቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፤ እነዚህን ጉዳዮች ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በሙሉ ተግባቦት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለተጎጂዎች ፈጣን የፍትህ ስርዓት እንዲያገኙ ለማድረግ መሰል ቅንጅታዊ ሥራዎች አስፈላጊ ናቸው።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኀላፊ አሰኬር መሐመድ በበኩላቸው የጋራ ተግባቦቱ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በጋራ ለመከላከል፣ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ነው።
በማንኛውም ጊዜና መነሻ የሚፈፀመውን ጥቃት ለመከላከልና ለመቀነስ በቀጣይነት ለሚሰሩ ስራዎችም ተግባቦቱ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ በመሳተፍ የጋራ ተግባቦት የፈጠሩት የክልሉ ፍትህ፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮዎች እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ሸሪአ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልሉ ወሳኝ ኹነቶች አገልግሎትና የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሰመራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ይገኙበታል።