የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለህዳሴው ግድብ ዳር መድረስ ያደረጉትን ድጋፍና መተባበር በሌሎች ልማቶችም አጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለህዳሴው ግድብ ዳር መድረስ ያደረጉትን ድጋፍና መተባበር በሌሎች ልማቶችም አጠናክረው ይቀጥላሉ

ድሬደዋ፣ መስከረም 6/2018(ኢዜአ):- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዳር መድረስ በህብረት ያሳዩትን መተባበርና ድጋፍ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ለመድገም እንደሚተጉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለፁ።
የአስተዳደሩ ነዋሪዎች የህዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቁን አስመልክተው ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች እንዳሉት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ የሀገራችንን መፃኢ ከፍታ የሚያረጋግጥ የጋራ ትጋት ውጤት ነው።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ አባድር አብደላ እና ወይዘሮ እመቤት ተሰማ እንደተናገሩት፤ ለህዳሴው ግድብ በህብረት ያሳዩትን ድጋፍና መተባበር በሌሎቹ ሀገራዊና የአስተዳደሩ ፕሮጀክቶች ላይ ለመድገም ይተጋሉ።
ወጣት ሰለሞን ሀብታሙ በበኩሉ የህዳሴው ግድብ መመረቅ ለሀገር ገንቢው እና ተረካቢው ወጣት ትውልድ ከፍተኛ ተስፋና መነቃቃት የፈጠረ ሀገራዊ የጋራ ውጤት መሆኑን ተናግሯል።
ወጣቱ በዚህ መነቃቃት በመታገዝ በህብረት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ከማስቀጠል በተጨማሪ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የድርሻውን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል።
ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያን መፃኢ ከፍታ ለማረጋገጥ ታሪካዊ ክስተት ፈጥረናል ያሉት ደግሞ መምህር አፈንዲ አባስ ናቸው።
የህዳሴ ግድብ በድል ተጠናቆ መመረቁ በሁላችንም ውስጥ ተስፋና ብርሃን ፈንጥቋል ያሉት መምህሩ፤ በቀጣይም የብልጽግና ጉዞውን ለማሳካት በተሻለ ደረጃ ተግተን እንሰራለን ብለዋል።
የፓናል ውይይቱን የመሩት አቶ ሙራድ በደዊ በበኩላቸው በተባበረ ህብረ ብሔራዊ አንድነት በመሄድ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በስኬት ማጠናቀቃችን በቀጣይም በራስ ዕውቀት፣ ሃብትና ጉልበት የትኛውንም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ማሳካት እንደምንችል ያረጋግጣል ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው የድሬዳዋ ነዋሪ ለህዳሴው ግድብ መሳካት በህብረት ያሳየውን ድጋፍና ቁርጠኝነት በሌሎችም ፕሮጀክቶች ላይ እንዲደግምም አስገንዝበዋል ።
የህዳሴው ግድብ መመረቅን አስመልክቶ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተካሄደ የሚገኘው ድጋፍና የደስታ መግለጫ እስከ መስከረም 12 ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ይቀጥላል።