ቀጥታ፡

የጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካህሳይ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዳማ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፦ የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካህሳይ ሥርዓተ ቀብር ወዳጅ ዘመዶቹ እና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት በአዳማ ቅዱስ መድኃኒዓለም ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈፀመ።

ጋዜጠኛ ገብረህይወት ካህሳይ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ለ30 ዓመታት ያክል ያገለገለ ሲሆን ባጋጠመው ድንገተኛ የጤና ችግር በትናንትናው እለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካህሳይ ከአባቱ አቶ ካህሳይ አብርሃ እና ከእናቱ ወይዘሮ በላይነሽ ቐለታይ በትግራይ ክልል በቀድሞው እንደርታ አውራጃ ታህሳስ 5 ቀን 1953 ዓ.ም ነበር የተወለደው።


 

ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ኢዜአን ከተቀላቀለበት ሐምሌ 1983 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ እስከተገለለበት ጥር 1/2013 ዓ.ም ድረስ በአሰላ እና አዳማ ቅርንጫፎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት ከሪፖርተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት አገልግሏል።

በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪው ያገኘው ገብረሕይወት ካሕሳይ በስራ ባልደረቦቹ የሚወደድና ታታሪ ጋዜጠኛም ነበር።

ከዜና ማጠናቀር ባሻገር በተለያዩ ርዕሶች የጻፋቸው በርካታ አርቲክሎችና ፊቸሮች በአዲስ ዘመን ጋዜጣና መጽሄቶች ለህትመት በቅተዋል።

ጋዜጠኛ ገብረህይወት ካህሳይ ኢዜአን ከመቀላቀሉ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የቦሊቦልና እጅ ኳስ ውድድሮች የቀድሞ የትግራይ ክፍለ ሀገርን ወክሎ በተደጋጋሚ ተሳትፏል፣ በርካታ ወጣቶችንም በማሰልጠን ለውጤት አብቅቷል።

ጋዜጠኛ ገብረህይወት ካህሳይ በማህበራዊ ሕይወቱ ተግባቢ፣ በስራ ባልደረቦቹ ተወዳጅ፣ በስራውም ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ታታሪ ጋዜጠኛ እንደነበር የስራ ባልደረባው ጋዜጠኛ በለጠ አድነው ይናገራል።

ሌላኛው የስራ ባልደረባው ጋዜጠኛ መታፈሪያ ግርማ፤ ጋዜጠኛ ገብረህይወት ካህሳይ በሙያው ምስጉንና ጠንካራ እና ለወጣት ጋዜጠኞችም አርአያ መሆኑን ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ገብረህይወት ካህሳይ ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም