በአቅራቢያችን በተገነባው ጤና ጣቢያ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እያገኘን ነው - የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በአቅራቢያችን በተገነባው ጤና ጣቢያ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እያገኘን ነው - የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮች

ጂንካ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ) :-በአቅራቢያቸው በተገነባው ጤና ጣቢያ ተገቢውን የህክምና አገልግሎትእያገኙ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለጹ፡፡
የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ(ዶ/ር) የተመራ የአመራር ቡድን በኛንጋቶም ወረዳ በቆላማ አከባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተገነባውን የቻሬ-ኮፒሪያይ ጤና ጣቢያ አገልግሎት አሰጣጥ ተመልክቷል።
የአካባቢው አርብቶ አደሮችም ጤና ጣቢያው በአቅራቢያቸው በመገንባቱ የወሊድና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው ከኮፕሪያይ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ጃካ ፓርቾ፤ ከዚህ ቀደም በአከባቢው ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ ረጅም ርቀት በእግር ተጉዘው ለህክምና ወደ ካንጋቴን ከተማ ይሄዱ እንደነበር ተናግረዋል።
በአከባቢው አመቺ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩም ነፍሰ-ጡር እናቶችን ወደ ካንጋቴን ጤና ጣቢያ ለመውሰድ በእጅጉ ይቸገሩ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ነዋሪ ሲኖ ዋላሲቦክ ናቸው።
ነፍሰ-ጡር እናቶችን ወደ ካንጋቴን ጤና ጣቢያ ለመውሰድ በሚያደርጉት ጥረት እናቶች በደም መፍሰስ አደጋ ይሞቱ እንደነበርና በፅንሱ ላይም አደጋ ይፈጠር እንደነበርም አስታውሰዋል።
ወይዘሮ ናስክሪያ ሎካፒቴ በበኩላቸው በአቅራቢያቸው ጤና ጣቢያ መገንባቱ የእርግዝና ክትትልና ወሊድን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሚሊዮን ተክሌ፥ ጤና ጣቢያው በ18 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በጀት የተገነባና ለአራት ቀበሌ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር የእናቶችና የህፃናት ሞት ለመቀነስ ብሎም ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ ባልሆነባቸው ጠረፍ አከባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሚኒስትር ዴኤታው እንድሪያስ(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በክልሉ በኛንጋቶም ወረዳ ሎከርለም ቀበሌ በግንባታ ላይ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመልክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንዳሉት በሀገሪቱ ቆላማ አከባቢዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
ከዚህ ውስጥ አንዱ ማሳያ በኛንጋቶም ወረዳ ሎከርለም ቀበሌ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ገልጸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የአከባቢውን ችግር ያገናዘበና ወሳኝ እንደሆነም አንስተዋል ።
በጉብኝቱ የዓለም ባንክ እና የሌሎች ድርጅቶች ተወካዮችም ተሳትፈዋል።