ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ649 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ

ጋምቤላ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ649 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ዙሪያ የፕሮጀክቱ የስትሪንግ ኮሚቴ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይቷል።


 

የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡቶው ኡኮት እንዳሉት ፕሮጀክቱ በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

በፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድና በሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ ማህበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎች ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል።

በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የጋምቤላ ክልል አስተባባሪ ቤል ቢቾክ(ዶ/ር) በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ባለፈው በጀት ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የህብረተሰቡን ህይወት የሚለውጡ የልማት ፕሮጅክቶችን አከናውኗል።


 

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ649 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በክልሉ ዘጠኝ ወረዳዎች የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ለማከናወን መዘጋጅቱን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑት የልማት ተግባራት መካከል የትምህርት፣ የእንስሳት ሀብት ልማት፣ የመንገድ፣ የአካባቢ ልማትና ጥበቃ፣ የጤና፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች መሳካት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም