የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ሌሎች ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን የመስራት አቅም እንዳለ የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ሌሎች ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን የመስራት አቅም እንዳለ የታየበት ነው

ደብረ ብርሃንና ገንዳ ውሃ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ሌሎች ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን የመስራት አቅም እንዳለ የታየበት መሆኑ ተገለጸ።
በአማራ ክልል ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄደዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ በህብረት ችለናል! በሚል ሃሳብ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል በደብረ ብርሃን እና በምእራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ የኢዜአ ሪፖርተሮች ያነጋገሯቸው ሰልፈኞች በስኬታችን ተደስተናል፤ ይህንንም ለመግለጽ ወደ አደባባይ ወጥተናል ብለዋል
በደብረ ብርሃን በሰልፉ ላይ ከተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አፀደ መስፍን እና አቶ ዓየለ ደስታ፤ የማይቻል ይመስል የነበረውን ስራ ችለንና አጠናቀን በማሳየታችን ደስታችን እጥፍ ደርብ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ስኬት ሌሎች ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም የመስራትና የማጠናቀቅ የተደመረ አቅም የታየበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፤ በጋራ ጥረታችን ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ የሁላችንም የደስታ ምንጭ ሆኗል ብለዋል።
የግንባታው እቅድ እውን እንዳይሆን ከውጭ ጫናዎች፤ ከውስጥ የበዙ መሰናክሎች ቢገጥሙም በጽናትና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ማሳካት ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ የተሳተፉት መላከ ኃይል ዘሚካኤል ሞገስ እና ሸክ አህመድ ኑርየ፤ የግድቡ መጠናቀቅ ለሀገራችን ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ሰላማችንን በማጽናት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሀመድ፤ የግድቡ የግንባታ ሂደት የሀገር ፍቅር በተግባር የታየበት የወል እሴትና የጋራ የደስታ ምንጭ ሆኗል ብለዋል።
የምእራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ፤ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ የእድገት መሰረቷን የጣለች መሆኗን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄደዋል።