ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ያሳየነው ቁርጠኝነት ዘመን ተሻጋሪ የታሪካችን አካል ነው - የጎንደር ከተማ አመራሮች እና ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ያሳየነው ቁርጠኝነት ዘመን ተሻጋሪ የታሪካችን አካል ነው - የጎንደር ከተማ አመራሮች እና ነዋሪዎች

ደብረ ማርቆስ /ወልድያ/ጎንደር ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ያሳየነው ቁርጠኝነት ዘመን ተሻጋሪ የታሪካችን አካል ነው ሲሉ የጎንደር ከተማ አመራሮች እና ነዋሪዎች ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱን ተከትሎ የጎንደር ከተማ ህዝብ በከተማው መስቀል አደባባይ በመውጣት ደስታውን ዛሬ በድጋፍ ሰልፍ ገልጿል፡፡
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የግድቡ መጠናቀቅ የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብን ለአገር እድገት፣ ለህዝብ መብራት፣ ለቀጠናው ማስተሳሰሪያ ገመድ ስላደረጉት ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ ሀሳብ አፍልቆ መተግበር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባው የጎንደር ከተማ ህዝብም ለህዳሴው ግድብ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት መሰረት ሽመልስ በበኩሉ የኢትዮጵያውያን ቁጭት የነበረው የአባይ ያለ ጥቅም መፍሰስ በግድቡ ግንባታ ታሪክ በመቀየሩ መደሰቱን ገልጿል።
አቶ ባዜ ተፈራ በበኩላቸው አባይ ተገድቦ ለልማት ሲውል በማየቴ እድለኛ ነኝ፤ ትውልዱም በዚህ ታላቅ ታሪክ ላይ አሻራውን በማሳረፉ የታሪኩ አካል ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ዳግማዊ አድዋ በመሆኑ ይህን አኩሪ ተግባር በማስቀጠል ሌሎች ልማቶችን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረ ማርቆስና በወልድያ ከተሞች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ህዝቡ በሠላማዊ ሠልፍ በአደባባይ በመውጣት ደስታውን ገልጿል።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲካ አቶ ዱባለ አብራሬ በራሳችን አቅም የተገነባው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ጥንካሬ መገለጫ ነው ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችን የደመቀበትና አንድነታችን ኃይል አመንጭቶ ብርሃን ያየንበት የአዲስ ዓመት ልዩ ስጦታ ነው ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ሀገረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስ፣ የደብረ-ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ አስተዳደር የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ- አቡነ ኤርሚያስ (ዶ/ር) በበኩላቸው አንድ ሆነን መስራት ከቻልን የማንገፋው ተራራ እንደሌለ የግድቡ መጠናቀቅ ህያው ምስክር ነው ብለዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አየነው ሃይሉ በሰጡት አስተያየት በራሳችን ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት የገነባነው ግድብ ከፍጻሜ ደርሶ በማየቴ ደስታዬ ወሰን የለውም ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ እንደገለጹት የግድቡ ለፍጻሜ መብቃት የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ያግዛል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን እውቀትና ጉልበት የተገነባ የአገር አንድነት ማህተም ነው ብለዋል።
በመተባበር የህዳሴ ግድብን እውን እንዳደረግነው ሁሉ በቀጣይም ተጨማሪ ልማቶችን ለማሳካት ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስና የጎዛምን ወረዳ የአባት አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ግርማ ታረቀኝ፤ የግደቡ መጠናቀቅ አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን ታሪክ በእኛ መደገሙን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፎቹ ላይ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባት አርበኞች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።