ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንጹህ ኢነርጂ ሽግግር ውስጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - የአፍሪካ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንጹህ ኢነርጂ ሽግግር ውስጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - የአፍሪካ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር በአፍሪካ የንጹህ ኢነርጂ ሽግግር ሂደት ውስጥ ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፍሪካ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሆንም ነው ብለዋል።
በሌሴቶ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩት እና በአፍሪካ ከሚገኙ አንጋፋ የቤተ መጻህፍት ባለሙያዎች መካከል አንዷ የሆኑት ቡህሌ ምባምቦ-ታታ (ዶ/ር) አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አስገራሚ የአረንጓዴ ኢኒሼቲቭ ተምሳሌት ናት ሲሉ ገልጸዋል።
መዲናዋ ይበልጥ አረንጓዴ እየሆነች የመጣችበት መንገድ እንዳስገረማቸው ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ እየተተከሉ ያሉ በርካታ ዛፎች ከተማዋን እንዳስዋቧት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የንጹህ ኢነርጂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችን ያደነቁት ባለሙያዋ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ይህንኑ ውጥን የሚያሳካ ነው ብለዋል።
ህዳሴ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት መመረቁ ይታወቃል።
ቡህሌ ምባምቦ-ታታ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የንጹህ ኢነርጂ ስራዋ በትክክለኛ መንገድ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግርን የበለጠ እንደሚያፋጥኑ ነው የገለጹት።
ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያን የጋራ ጥረት የተሳካ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፀሐይን ጨምሮ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጮችን በመጠቀም ብክለትን ለመቀነስ እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
የጋና ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ስተዲስ የትምህርት ክፍል መምህር እና የዓለም አቀፍ የቤተ መጻህፍት ማህበራት እና ተቋማት ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ሞኒካ ሜንሳህ ዳንኩዋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየወሰደቻቸው የሚገኙ እርምጃዎችን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ የአየር ንበረት ለውጥ መፍትሄዎች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም መተግበር እንደሚገባቸው እና ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዋችውን መለዋወጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
አፍሪካውያን ከአህጉሪቷ ውጪ ያሉ መፍትሄዎችን ከመጠበቅ ይልቅ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን ገቢራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።