በአማራ ክልል የተካሄደው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ሕዝብ ቃሉም ተግባሩም ለልማት የወገነ መሆኑን ያሳየበት ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተካሄደው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ሕዝብ ቃሉም ተግባሩም ለልማት የወገነ መሆኑን ያሳየበት ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተካሄደው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ሕዝብ ቃሉም ተግባሩም ለልማት የወገነ መሆኑን ያሳየበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ሕዳሴ ከሁሉም ማዕዘናት ወደ አንድ ሀገራዊ የልማት ዕሳቤ እየተደመሩ ኃያል የመሆን እና የመተባበር ህያው ምልክት ነው ብለዋል።
ዛሬ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝቡ ያሳየው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ገጸ ብዙ ትርጉም ያለው ሰልፍ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም የክልሉ ሕዝብ ቃሉም ተግባሩም ለልማት የወገነ መሆኑን ማሳየቱን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተስተዋለው የዛሬው ሰልፍ እንደ ዓባይ ለታላቅ ግብ የመደመር፣ ፈተናዎችን እያሸነፉ መሻገር፣ ለልማት የተከፈለን መስዋዕትነት የማክበር የከበረ የሕዝብ ድምጽ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እንደዚህ ያሉ የሕዝብ ታላላቅ ሰልፎች ለቀጣይ የኢትዮጵያ ግዙፍ ልማቶች የሚያተጋን የብርታት ደውል ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሰፈሩት መልዕክት።