ቀጥታ፡

የአንድነታችን ምንጭ የሆነው ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታችን ወደር የለውም - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ፤ መስከረም 6/2018 (ኢዜአ)፦ የሉዓላዊነታችን መገለጫ፣ የአንድነታችን ምንጭ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታችን ወደር የለውም" ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክቶ የደሴ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ገልጸዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ እንድሪስ መሀመድ በሰጡት አስተያየት የሕዳሴ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታችንን አደባባይ ወጥተን በመግለጽ ላይ ነን ብለዋል።


 

በሕዳሴው ግድብ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያሳየነውን ተነሳሽነት ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በመጠቀም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ አያሌው ሀሰን በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ እንዲበቃ በቦንድ ግዢ  አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት፣ የአንድነታችን ማህተም፣ የሁለተናዊ ብልጽግናችን ጅማሮ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሉዓላዊነታችን መገለጫ፣ የአንድነታችን ምንጭ የሆነው ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታችንን እየገለጽን ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰላማዊት ጋሻው ናቸው።

ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ኢክራም ሰይድ፤ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አቅደን በጋራ እንድንሰራ መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።


 

አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ከመንግስት ጋር ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመቆም እንደሚችል ያሳየበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በግንባታ ሂደቱና ከተጠናቀቀ በኋላም አንድነትን ያጠናከረና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ያስከበረ ታሪካዊ የድል ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ ለሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመው በግድቡ መመረቅም የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በሰልፉ ላይ የሐይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም