ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝብን በማሳተፍ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝብን በማሳተፍ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው

አዳማ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝብን በኅብረት በማሳተፍ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው ሲሉ የአዳማ ከተማ አመራሮች እና ነዋሪዎች ተናገሩ።
የግድቡን መመረቅ ተከትሎ የአዳማ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የከተማዋ ነዋሪዎች ደስታቸውን ለመግለጽ ዛሬ ማለዳ በጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አካሂደዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ እንደገለጹት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝብን በኅብረት በማሳተፍ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ የጋራ ስኬት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሰፋ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግድቡን ለፍጻሜ ለማድረስ መላው የከተማ ነዋሪና አስተዳደሩ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እመቤት ጅባ በሰጡት አስተያየት ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ የህዝብን ቁጭት ወደ ደስታ መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።
በጋራ ጥረት እውን የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አሜን ዘመድኩን ነው።
ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን በመፍታት ለልማቱ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አስረድቷል።