ቀጥታ፡

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የአቪዬሽን ማዕከል ያደርጋታል -ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የአቪዬሽን ማዕከል እንደሚያደርጋት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገነባውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር እያከናወነ ነው።


 

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአውሮፕላን ማረፊያው የህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች እና ተቋራጮች እንዲሁም የተለያዩ  ሀገራት ዲፕሎማቶች እና የፋይናንስ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን መሻት የሚያሳካ ዓለም አቀፍ ትስስር እና ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።በተጨማሪም የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።


 

አውሮፕላን ማረፊያው ከመጓጓዣ አገልግሎት በላይ የሆነ ለትስስር፣ ለቀጣናዊ ዕድገት፣ ለቱሪዝም፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ስትራቴጂያዊ መሪ መሆኑን አመላክተዋል። 

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ግዙፉ ይሆናል ብለዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ያለውን ጫና እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የአቪዬሽን ማዕከል እንደሚያደርጋት አመላክተዋል።

ሁለቱን አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚያገናኝ ልዩ የፍጥነት ባቡር መስመር እንደሚዘረጋ ገልጸው ይህም ፈጣን የመንገደኞች አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ አፍሪካን ከዓለም የማስተሳሰር ዓላማ በማንገብ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። 


 

ባለፉት ዓመታት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየጨመረ የመጣውን የመንገደኛ ፍሰት ለማስተናገድ በርካታ ማስፋፊያዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓመት 25 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ መድረሱን አመላክተዋል።

አየር መንገዱ ዕድገቱን በማስቀጠል ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ አዲስ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት መወሰኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ ለመጀመር አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች ሁሉ ሲከናወኑ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፥  ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የአፍሪካን ዕድገት፣ ጥንካሬ እና አንድነት ያጎለብታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም