ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ታሪክ እንደምንሰራ ዳግም በህዳሴው ግድብ አስመስክረናል-የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ታሪክ እንደምንሰራ ዳግም በህዳሴው ግድብ አስመስክረናል-የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች
ሰቆጣ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ታሪክ እንደምንሰራ ዳግም በህዳሴው ግድብ አስመስክረናል ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የከተማው ነዋሪዎች የህዳሴው ግድብ ለምረቃ መብቃቱን ተከትሎ ደስታቸውን አደባባይ በመውጣት ገልፀዋል።
የሰቆጣ ከተማ ነዋሪና የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ግርማይ ፈለቀ እንደገለፁት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር በግና ፍየል በማበርከት ለግድቡ እውን መሆን የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።
አሁን ላይ የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ በማየታቸው የዘመናት ቁጭታቸውን እንደተወጡ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ታሪክ እንደምንሰራ ዳግም በህዳሴው ግድብ አስመስክረናል ሲሉ አቶ ግርማይ ገልፀዋል።
ሌላው ተሳታፊ መልዓከ አርያም ቀሲስ ደሴ የማነብርሃን በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ለፍፃሜ እንዲደርስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በአንድነት ያለውን አስተዋፅኦ ያበረከተበት ነው ብለዋል።
"አባይ ተገድቦ በእድሜዬ በማየቴ እድለኛ ነኝ" ያሉት መልዓከ አርያም ቀሲስ ደሴ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተባበርን ታሪክ መስራት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወጣቱ ትውልድም አሁን እየተመዘገበ ያለውን የልማት ውጤት ለማስቀጠል የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የህዳሴው ግድብ እስኪጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አውስተው አሁን ላይ ግድቡ ለምረቃ በመብቃቱ ደግሞ ድርብ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ፤ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ግዙፍ ፕሮጀክትን ማሳካት እንደሚቻል ለአለም ያሳየበት ነው ብለዋል።
"የተፈጥሮ ሃብታችንን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታችንንም አረጋግጦልናል" ያሉት አቶ ጌትነት የአድዋን ታሪክ የአሁኑ ትውልድ በህዳሴው ግድብ ደግሞታል ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው ግድቡ ምስራቅ አፍሪካን በኤሌክትሪክ ሃይል የሚያስተሳስር የትብብር ተምሳሌት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።