ቀጥታ፡

ሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ ያርፉበት የነበረው ቤት የቅርስነት ደረጃውን ጠብቆ  ሊታደስ ነው

ሰመራ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- ሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ ለስራ ሲንቀሳቀሱ ያርፉበት የነበረው ቤት የቅርስነት  ደረጃውን ጠብቆ ሙሉ ዕድሳት ሊደረግለት መሆኑን የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

በአፋር ክልል አውሲ ራሱ ዞን ኤሊዳአር ወረዳ ለፈፍሌ በተሰኘ ስፍራ የሚገኘው ታዋቂው ሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ እረፍት ያደርጉበት የነበረው ቤት የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ሙሉ ዕድሳት ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል።


 

የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ እንዳሉት ሱልጣን አሊሚራህ በዘመናቸው ለማረፊያነት ይጠቀሙበት የነበረው ቤት የቅርስነት ደረጃው ተጠብቆ ሙሉ ዕድሳት ተደርጎለት ለጎብኚዎች ክፍት ይደረጋል።


 

የህንፃው እድሳት በክልሉ መንግስትና በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በትብብር የሚከናወን ሲሆን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃ መሆኑንም ተናግረዋል።

የህንፃው እድሳት በድምሩ 30 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ  መሆኑንም ገልጸዋል ።

በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ አብዱ አህመድ፤ ይህ ማረፊያ ከሶስት አቅጣጫ ከጅቡቲና አሰብ የሚመጡ አባቶች የሚገናኙበት ዕድሜ ጠገብ ስፍራ እንደነበር አንስተዋል።


 

በጊዜው ሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ አይሳኢታ ከሚገኘው ቤተ መንግስታቸው ተነስተው ለማረፊያነት የሚገለገሉበት ሲሆን ወደ አሰብና ጅቡቲ ለሚደረገው ጉዞ ያገለግል እንደነበርም አስታውሰዋል።

ህንፃው ታድሶ አገልግሎት ሲጀምር የጎብኝዎችን ፍሰት በመጨመር ረገድ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የኤሊዳአር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ ሱሌ ናቸው።


 

ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንዲሆንና ዕድሳት እንዲደረግለት መወሰኑንም አንስተዋል።

በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ታሪካዊው ህንፃ ከጅቡቲ 130 ኪሎ ሜትር፣ ከአሰብ ደግሞ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም