በምስራቅ ቦረና ዞን የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለቤት እንስሳት ክትባት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለቤት እንስሳት ክትባት እየተሰጠ ነው

ነገሌ ቦረና ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- በምስራቅ ቦረና ዞን የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባለፉት ሁለት ወራት ለቤት እንስሳት ክትባት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ምስራቅ ቦረና ዞን በኦሮሚያ ክልል በብዛት የእንስሳት እርባታ ከሚካሄድባቸው ዝናብ አጠርና ቆላማ ዞኖች መካከል የሚጠቀስ ነው።
በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ጤና ቡድን መሪ አቶ ዲዶሌ ሊበን፤ ክትባቱን ለበርካታ የቤት እንስሳት ለመስጠት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
ክትባቱ እየተሰጠ ያለው ነገሌ ቦረና ከተማን ጨምሮ በዞኑ ዘጠኝ ቆላማ እና ዝናብ አጠር ወረዳዎች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ700 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት ክትባት ማግኘታቸውን አመልክተዋል።
እስካሁን ክትባቱን ከወሰዱ የቤት እንስሳት መካከል 72 ሺህ 248 የቀንድ ከብቶችና 103 ሺህ 325 ፍየሎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ክትባቱ የሚሰጠው የእንስሳት ሳንባ ምች፣ አባ ሰንጋ፣ አባ ጎርባ፣ የምላስና የቆዳ በሽታ የመሳሰሉትን የጤና ችግሮች አስቀድሞ ለመከላከል መሆኑን ጠቅሰው ክትባቱ የቀንድና የጋማ ከብቶችን፣ ግመሎችን፣ ፍየሎች፣ በጎችና ዶሮዎችን የሚያካትት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡