በሲዳማ ክልል ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ የማድረግ ስራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ የማድረግ ስራ ተሰርቷል

ሀዋሳ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ትምህርት ቤቶችን ምቹ የማድረግና በቁሳቁስ የማሟላት ስራ መሰራቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የ2018 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራ ዛሬ በክልሉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በመቀበል ተጀምሯል።
በሲዳማ ክልል የ2018 የትምህርት ዘመን ዝግጅትና የመማር ማስተማር መጀመርን በተመለከተ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አቶ በየነ በቆይታቸውም እንዳሉት በክረምቱ ወቅት ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ስራ ምቹ የማድረግ፣ በቁሳቁስ የማሟላትና የማደረጀት ስራ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
መላው የክልሉ ማህበረሰብ፣ ሰራተኞች፣ ባለሀብቶችና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት በዕድሳት፣ በጥገናና አዲስ በመገንባት ረገድ በንቃት እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም 78 ቅድመ አንደኛና 4 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመንግስትና በማህበረሰቡ ትብብር መገንባት እንደተቻለ ተናግረዋል።
ነባር ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ስራ ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ የማድረግና በግብዓት የማሟላት ስራ በክረምት ወቅት መጠናቀቁን ገልጸው በዋናነት የመጽሃፍት ተማሪ ጥምርታን ለማመጣጠን በትኩረት መሰራቱንም አስረድተዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት አቶ በየነ ማህበረሰቡ በቅርበት በመስራት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።
የሀዋሳ ታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ወንዳቸው ውለታ እንዳሉት ትምህርት ቤቱን ለትምህርት ስራ ምቹ የማድረግ ስራ በክረምቱ ወቅት ተጠናቆ ዛሬ የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሯል።
ቤተ መጽሀፍትን፣ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የቤተ ሙከራዎችንና የኮምፒውተር ክፍሎችን የማደስ፣ በቁሳቁስ የማሟላት፣ የተሰበሩትን የመጠገንና በአዲስ የመተካት ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
በትምህርት ቤቱ የስነ-ዜጋ ትምህርት መምህር መንግስቱ ጴጥሮስ በበኩላቸው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን በክረምት ወቅት የማስተማሪያ ዕቅድ እንዳዘጋጁና በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የመምህራን ስልጠና ወስደው በአዲስ መንፈስ ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ስራውን የሚያሳልጡ ግብዓትን በማሟላትና ከአምናው የተሻለ ዝግጅት በማድረግ ማስተማር ጀምረናል ነው ያሉት።
በትምህርት ቤቱ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ በረከት በቀለ ትምህርት ቤቱ ታድሶ ምቹ መሆኑ እና በክረምት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሰጠውን የማጠናከሪያ ትምህርት ስከታተል ቆይቻለሁ፤ ዘንድሮ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።