ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም እንደምትችል ያረጋገጠ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህርዳር፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም እንደምትችል ያረጋገጠ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት  የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም እንደምትችል ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ግንባታው በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት የሚቻል መሆኑን  እና በህብረ ብሔራዊ አንድነት የላቀ ውጤት፣ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፤ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የግድቡ ግንባታ ስኬት የዘመናት ቁጭት ያበቃበት፤ ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረት እየተሳካ መምጣቱን  እንዲሁም  የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል። 

ከማለዳው ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን በማንገብ ደስታቸውን አስተጋብተዋል።

በመፈክሮቻቸውም የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክት ነው፣ የብልጽግናችን አሻራ፣ የሚጨበጥ ብርሃን ያየንበት ነው፤ በራስ አቅም የተገነባ የሀገር ሃብትና የአፍሪካ ኩራት መሆኑን የሚያሳዩ ፅሁፎች ተስተጋብተዋል።

የአባይ ዘመን ትውልድ አኩሪ ገድል፤ የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መሰረት እንዲሁም የማንሰራራት ጅማሮ ነው የሚሉም እንዲሁ።

በአማራ ክልል ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም