ቀጥታ፡

አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በ1 ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ ትወዳደራለች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6 /2018 (ኢዜአ)፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ዛሬ በሚካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ኢትዮጵያን ወክላ ትወዳደራለች።

ውድድሩ ከቀኑ 10 ሰዓት ከ 05 ላይ ይካሄዳል።

አትሌት ፍሬወይኒ ለዛሬው ፍጻሜ የደረሰችው የሁለት ዙር ማጣሪያዋን በብቃት በመወጣቷ ነው።

ፍሬወይኒ እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1 ሺህ 500 ሜትር ፍጻሜ ተወዳድራ አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

አትሌቷ እ.አ.አ በ2023 በኢውጅ በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች። 

ፍሬወይኒ እ.አ.አ በ2024 በግላስኮው በተደረገው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1 ሺህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ አይዘነጋም።

በዛሬው የፍጻሜ ውድድር ላይ 14 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ35 በሚካሄደው የ800 ሜትር ወንዶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አትሌት ዮሐንስ ተፈራ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል።

በምድብ ስድስት የሚወዳደረው አትሌት ዮሐንስ እ.አ.አ ጁላይ 5, 2025 በፈረንሳይ በተካሄደ ውድድር 1 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ49 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

በሰባት ምድብ በሚካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ አትሌቶች ለግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ።

አራተኛ ቀኑን በያዘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስከ አሁን ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም