ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል

አምቦ፤ ጊምቢ/ መቱ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- በምዕራብ ሸዋ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የ2018 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት በኤጀርሳ ለፎ ወረዳ በገባ ዲልበታ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትናንት ተጀምሯል።


 

በዚሁ ጊዜ የምዕራብ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንዲራ ጋላና፤ የትምህርት ዘመኑን ውጤታማ ለማድረግ በክረምቱ ወራት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች እና ዲጂታል ቤተ-መጽሃፍት መገንባታቸውን ተናግረዋል።


 

በክረምቱ ወራት የተገነቡ የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በትምህርት ዘመኑ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በተያዘው የትምህርት ዘመንም በዞኑ በሚገኙ 2 ሺህ 167 የትምህርት ተቋማት 700 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይሆናሉ ብለዋል።

የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ ፍቅሬ በበኩላቸው በወረዳው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ጀምረዋል።


 

በዚህም በወረዳው በትምህርት ዘመኑ 17 ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት መጀመራቸውን ገልጸው የመማር ማስተማር ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

በወረዳው በሚገኝ  ኦልማ አዳ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት የሆኑት በየነች ቀቀባ በበኩላቸው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቱ ስራ መጀመሩ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል።


 

በመሆኑም ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ዕድሜያቸው ለቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በወረዳው የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሀና ማሞ፤ በክረምት ወቅት የማጠናከሪያ ትምህርት ስትማር ማሳለፏን ገልጻ በመደበኛውም ትምህርቷን በአግባቡ ለመከታተል መዘጋጀቷን ገልጻለች።


 

በተመሳሳይም የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራ በምዕራብ ወለጋ እና በኢሉአባቦር ዞኖችም በትናንትናው እለት ተጀምሯል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት የቅደመ መደበኛ ትምህርት ምዘና ባለሙያ አቶ ከኔሳ ከበደ ለኢዜአ እንደተናገሩት የ2018 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሯል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን በዞኑ ከ540 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ለማስተማር ዝግጅት መጠናቀቁን አውስተዋል፡፡

በዞኑ 595 የቅድመ መደበኛ፣ 849 የአንደኛና 102 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው በክረምቱ ወራት የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ የማሻሻል ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።


 

በኢሉአባቦር ዞን በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ ከ1ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ ዛሬ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጎበና አለማየሁ አስታውቀዋል።

በዚህም በዞኑ በ1 ሺህ 35 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው መደበኛ ትምህርት የተጀመረ ሲሆን  በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ ስራው መጀመሩን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም