በኦሮሚያ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይስፋፋ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይስፋፋ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

አዳማ ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- በኦሮሚያ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይስፋፋ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በአሁኑ ጊዜ በመጀመሪያው ዙር 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱም ተመላክቷል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው ለኢዜአ እንዳሉት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተደራጀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም የወባ ትንኝን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን የማፍሰስ እና የጽዳት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የዜግነት አገልግሎትን በመጠቀም የወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ቤት ለቤት የወባ ቅኝት ስራዎች በማከናወን ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የወባ መከላከል ዘዴዎችን በጤና ተቋማት፣ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎችና ቤት ለቤት ጭምር የማስተማር ስራዎችም መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተመረጡ አካባቢዎች የኬሚካል ርጭት እንደሚካሄድ ጠቅሰው እስካሁን በኢሉባቡር፣ ምእራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች ቤት ለቤት የኬሚካል ርጭቱ መካሄዱን ገልጸዋል።
እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱን ገልጸው፤ እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅርቡ ለህብረተሰቡ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ተጨማሪ የአልጋ አጎበሮችን ለማሰራጨት መታቀዱንም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡም የተሰጠውን የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።
አሁን ላይም የወባ በሽታን ለመቆጣጠር እየተሰጠ ያለው ምላሽ እስከ ወረዳ ድረስ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡