ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ በመደመርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ለላቀ ስኬት መብቃት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፤ መስከረም 6/ 2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመደመር እና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ለላቀ ስኬት መብቃት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ጥረት ላለፉት 14 ዓመታት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ይታወቃል።

በአፍሪካ በግዙፍነቱ የሚጠቀሰው ግድብ የተለያዩ አገራት መሪዎችና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እንዲሁም ሌሎች ታዳሚዎች በተገኙበት ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ጥሪታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታችውን ጭምር በመፍቀድ ያለማንም እገዛ እውን ያደረጉት ፕሮጀክት በመሆኑ ከምረቃው እለት ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች ዜጎች ደስታቸውን መግለፃቸውን ቀጥለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመደመርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ለላቀ ስኬት መብቃት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደ ተጨባጭ ለውጥና ብርሃን የመሸጋገርና የማንሰራራት ሂደት ላይ መሆኗ የተበሰረበት ስለመሆኑ አንስተዋል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በቀጣይ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት፤ እውቀትና ክህሎትም ያካበትንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከውጭ በነበረ ብርቱ ጫና እና በውስጥ በነበሩ ፈተናዎች ባለመረታት ለተገነባው ግዙፍ ፕሮጀክት የመንግስት ቁርጠኝነት፣ የመሪነት ጥበብና የመፈፀም አቅም እንዲሁም የህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ የታየበት ስለመሆኑ አንስተዋል። 

በመሆኑም በተመዘገቡ ስኬቶች በመነቃቃት በቀጣይ ለላቀ የልማት እድገትና ማንሰራራት በጋራ መትጋት አለብን ሲሉ ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም