ቀጥታ፡

የጥርስ ህመም እና መከላከያዎቹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2018(ኢዜአ)፡- በፈረንጆቹ 2025 ለዓለም ጤና ድርጅት የቀረበ ሪፖርት እንደሚያመላክተው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሰዎች ለጥርስና ከጥርስ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ህመሞች ተናጋላጭ ናቸው።

በኢትዮጵያም ለጥርስና ከጥርስ ጋር ለተያያዙ ህመሞች ተጋላጭ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን እአአ ከ2021 እስከ 2025 የተካሄዱ ጥናቶች ማመላከታቸውን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአፍና የጥርስ ሐኪም እና መምህርት ዶክተር ካሰች አያሌው ተናግረዋል።

የጥርስ እና ተያያዥ ህመሞችን ቀድሞ እንዴት መከላከል እንደሚቻል እና በህመም ላይ ከሆኑም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ዶክተር ካሰች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።

👉 የጥርስ ህመም ማለት …

ዶክተር ካሰች እንዳሉት፤ የጥርስ ህመም ማለት በጥርስ እና በጥርስ አቃፊ(ደጋፊ) ዙሪያ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። ለምሳሌ፡- ጥርስን የሚደግፉ የድድ፣ የአቃፊ አጥንትና ሥር ህመም ሁሉ በጥርስ ህመም ውስጥ ይጠቃለላሉ።

👉 የጥርስና ተያያዥ ህመም ዓይነቶች…

• የጥርስ መቦርቦር (ዴንታል ኬሪስ)፤

• ከድድ ጋር የተያያዙ (የድድ መቆጣት፣ የድድ መሸሽ)፤

• የከንፈር እና የአፍ ውስጥ ካንሰር፤

• የጥርስ፣ መንጋጋ እና መንገጭላ ስብራት ወይም ውልቃት፤

• የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ መሆናቸውን ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

👉 ለጥርስ ህምም ተጋላጮች…

• በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ለጥርስና ተያያዥ ለሆኑ ህመሞች እንደሚጋለጡ ጠቁመው፤ በዋናነት በተወሰነ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች በተወሰኑ የጥርስና ከጥርስ ጋር ተያያዥ በሆኑ ህመሞች ይጠቃሉ ብለዋል።

• በተለይም ሕጻናት እና ወጣቶች ለጥርስ መቦርቦርና ከጥርስ ጋር ለተያያዘ ህመም ተጋላጭ መሆናቸውን አስረድተዋል።

• በተጨማሪም በዕድሜ የገፉ ሰዎች በአብዛኛው ለጥርስ ሥር መቦርቦር ተጋላጭ መሆናቸውን ነው ባለሙያዋ የገለጹት።

• በሌላ በኩል የከንፈር እና የአፍ ውስጥ ካንሰር እንዲሁም የድድ ችግር በወንዶች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል።

👉 የጥርስ ህመም መንስዔ…

• ለጥርስና ተያያዥ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ካሰች፤ ከእነዚህ መካከል፡- የጥርስ ባክቴሪያ፣ የተመጣጠነ አመጋገብ አለመኖር(ጣፋጭ ምግቦችን ማዘውተር)፣ በትጋት የአፍ ንጽህናን አለመጠበቅ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም እና አደጋዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

• በተጨማሪም ጭንቀት፣ የሆርሞን ተጽዕኖ፣ የውስጥ የጤና ሁኔታ መታወክ (ለምሳሌ፡- የልብ፣ የኩላሊት፣ የላይኛው መተንፈሻ አካል እና የስኳር ህመም)፣ በዘር ሐረግ የመተላለፍ ሁኔታ፣ በቂ ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙና አለመጠቀምና የብሩሽ ንጽህና መጓደልን ዘርዝረዋል።

👉 የጥርስ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ…

• የአፍ እና የጥርስ ንጽህናን መጠበቅ (ከቁርስና ከእራት በኋላ በቀን ሁለት ጊዜ ከ3 እስከ 5 ደቂቃ ጥርስን መቦረሽ)፣ አመጋገብን ማስተካከል(ጣፋጭ ምግቦችን አለማዘውተር፤ ለጥርስ ጤና ጠቃሚ ምግቦችን መመገብ)፣ ቢያንስ በ6 ወር አንድ ጊዜ የአፍ ውስጥ ጤና ምርመራ ማድረግ፤ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጎዱ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ካሉ አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ማድረግ ለጥርስ ህመም የመጋለጥ ዕድልን እንደሚቀንሱ አስገንዝበዋል።

👉 የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች…

• ባለሙያዋ እንዳሉት፤ የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ያለውን የህመም ሁኔታ በምርመራ አረጋግጠው የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

• ህመሙ እንዳይባባስ የአመጋገብ ሁኔታን ማስተካከል እንዲሁም ጨው የተጨመረበት ለብ ያለ ውኃን በመጠቀም ከምግብ በኋላ አፍን መጉመጥመጥ እንደሚመከርም ገልጸዋል።

👉 ሕክምናው…

• የጥርስና ተያያዥ ህመም ሕክምና ህመሙ እንደተከሰተበት ቦታ፣ እንደ ህመሙ ቅለትና ውስብስብነት በምርመራ ተለይቶ ከጊዜያዊ እስከ ዘላቂ ሕክምናዎች እንደሚሰጥ ዶክተር ካሰች ገልጸዋል። ሕክምናው ጥርስን ባለበት ከማከም በነቀላ እስከማስወገድ እንደሚደርስም ጠቁመዋል።

👉 በአጠቃላይ ስለ ጥርስና ተያያዥ ህመሞች

• በፈረንጆቹ 2025 ለዓለም ጤና ድርጅት የቀረበ ሪፖርትን በዋቢነት የጠቀሱት ዶክተር ካሰች፤ በዚህ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሰዎች ለጥርስና ተያያዥ ህመም ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል ብለዋል።

• ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘውም የጥርስ መቦርቦር (መበስበስ) የሚባለው የጥርስ ህመም ዓይነት መሆኑን አንስተው፤ ከአጠቃላዩ 3 ነጥብ 2 ቢሊየኑ ሰዎች በዚህ ህመም እንደሚሰቃዩ ገልጸዋል። 514 ሚሊየን ሕጻናትም የጥርስ መቦርቦር እንዳጋጠማቸው አንስተዋል።

• በሁለተኛነት ከጥርስ ህመም ጋር በተያያዘ የተቀመጠው ጥርስን የሚደግፉ የድድ፣ አቃፊ አጥንት እና ሥር ህመም መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከ1 ቢሊየን በላይ ሰዎች እንደሚጠቁ ጠቁመዋል።

• እንዲሁም ከ2021 እስከ 2025 የተካሄዱ ጥናቶች እንዳመላከቱት በኢትዮጵያ የጥርስና ተያያዥ ህመሞች እየጨመሩ ነው ያሉት ባለሙያዋ፤ ከአጠቃላይ ሕዝቡ በአማካይ 41 በመቶው የጥርስ መቦርቦር ህመም ተጠቂ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም