ኮሚሽኑ አዳዲስ ሰራተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱ ተልዕኮውን በሚገባ ለመወጣት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል- ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ አዳዲስ ሰራተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱ ተልዕኮውን በሚገባ ለመወጣት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል- ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ ጉምሩክ ኮሚሽን አዳዲስ ሰራተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱ ተልዕኮውን በሚገባ ለመወጣት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥሩለት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ።
የጉምሩክ ኮሚሽን የአዳዲስ የጉምሩክ ሠራተኞች የምረቃ መርሃግብር አካሄዷል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በዚሁ ወቅት የጉምሩክ ኮሚሽን የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፍ አበረታች ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ እሳቤዎች ስራውን ተግባራዊ የሚያደርግና ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ አዲስ ሰራተኞች ኮሚሽኑን መቀላቀላቸው ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ገልፀዋል።
በዚህም ሰራተኞቹ የተቋሙን ሀገራዊ ተልዕኮ በሚገባ በመረዳት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላችው፤ ኮሚሽኑ ከለውጡ ወዲህ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመልምለው ስልጠና እና የብቃት ፈተና ወስደው ያለፉ ከ3 ሺህ 200 በላይ አዲስ የጉምሩክ ባለሙያዎችን አስመርቋል ብለዋል።
እነዚህ አዲስ ሠራተኞች ከዛሬ ጀምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት እውን መሆን ጉልህ አሻራቸውን እንደሚያሳርፉ ተናግረዋል።
አዲስ ሠራተኞች በታማኝነት፣ በትህትና እና በትጋት ሀገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) እንደሀገር የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ማሻሻያ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑም እያከናወነ ያለው ስራ አበረታች እንደሆነ አንስተው፤ ምልመላ ብቃትና አካታችነትን መሰረት ያደረገ ሲሆን ለሀገር መንግስት ግንባታ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞቹ በቆይታቸው የተቋሙን ተልዕኮ መወጣት የሚያስችል እውቀት እንዳስጨበጣቸው ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት አዲስ የተቋሙ ሰራተኞች ሀገርን በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለማሳካት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።