የኢዜአ የቀድሞ ባልደረባ ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካሕሳይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ የቀድሞ ባልደረባ ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካሕሳይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ለ30 ዓመታት ያክል በጋዜጠኝነት ያገለገለው ገብረሕይወት ካሕሳይ ባጋጠመው ድንገተኛ የጤና ችግር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ጋዜጠኛ ገብረሕይወት ካህሳይ ከአባቱ አቶ ካህሳይ አብርሃ እና ከእናቱ ወይዘሮ በላይነሽ ቐለታይ በትግራይ ክልል በቀድሞው እንደርታ አውራጃ ታህሳስ 5 ቀን 1953 ነበር የተወለደው።
ጋዜጠኛ ገብረሕይወት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ከተቀላቀለበት ከሐምሌ ወር 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለለበት ጥር 1/2013 ዓ.ም. ድረስ ከሪፖርተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት በሙያው አገልግሏል።
በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ የነበረው ገብረሕይወት ካሕሳይ በስራ ባልደረቦቹ የሚወደድ ታታሪ እና ጎበዝ ጋዜጠኛም ነበረ።
ባለትዳርና የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆነው ገብረሕይወት ካሕሳይ የቀብር ስነስርዓት በነገው እለት በአዳማ ከተማ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ከቀኑ 6፡00 ሰዓት እንደሚፈጸም ከቤተሰቡ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በገብረሕይወት ካሕሳይ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቡ፣ ለሙያ አጋሮቹና ወዳጆቹ መጽናናትን ይመኛል።