ቀጥታ፡

ዓላማ ሰንቄ በርትቼ ማጥናቴ ለስኬት አብቅቶኛል -ተማሪ ካሊድ በሽር

ሮቤ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ ዓላማ ሰንቄ በርትቼ ማጥናቴ ለስኬት አብቅቶኛል ሲል በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ተማሪ ካሊድ በሽር ተናገረ።

በኦሮሚያ ክልል የዶዶላ ኢፈ ቦሩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ካሊድ በሽር በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 591 በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ 

ተማሪው የእንግሊዝኛ ትምህርት 96፣ በሂሳብ 100፣ በፊዚክስ 100፣ በኬሚስትሪ 98፣ በባዮሎጂ 99፣ በአፕቲትዩድ 98 ያስመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ 591 ከ600 አምጥቷል። 

ጠንካራውና ውጤታማው ተማሪ ካሊድ በተለይም የቁጥር ቀመር የሚበዛባቸውን ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ በመስራትና በመድፈን አስደናቂነቱን አሳይቷል።

ተማሪ ካሊድ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት በማምጣቱ ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ገልፆ ዓላማ ሰንቄ በርትቼ ማጥናቴ ለስኬት አብቅቶኛል ብሏል።

የስኬቱ ምስጢርም ለትምህርቱ የላቀ ትኩረት በመስጠት ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በማጥናቱ፣ በክፍል ውስጥ ትምህርቱን በአግባቡ በመከታተሉና ያልገባውን ሁሉ መምህራኑን ጠይቆ በመረዳቱ መሆኑን ተናግሯል።

ከመማሪያ መጽሃፍት ባሻገር ብዙ ማጣቀሻዎችን የያዘ የዲጂታል ቤተመጻህፍት ቋትን በሞባይሉ እንደሚጠቀምና ለስኬቱ በእጅጉ እንዳገዘውም አንስቷል።

ሌሎች ተማሪዎችም ዓላማቸውን ሳይለቁ ለትምህርታቸው ጊዜ ከሰጡ የፈለጉትን ውጤት ማምጣት ይችላሉ ያለው ተማሪ ካሊድ በቀጣይም ለላቀ ስኬት የሚዘጋጅ መሆኑን አረጋግጧል።

ከህጻንነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ ልዩ ዝንባሌ እንዳለው በማንሳት በዩኒቨርሲቲ በሚኖረው ጊዜም የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ በመማር ሀገሩን በዘርፉ ለማገልገልና ስኬታማ ለመሆን እንደሚሰራም ተናግሯል።

በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ጎባ ክፍለ ከተማ የተወለደው ተማሪ ካሊድ፤ በ2013 ዓ.ም ከ8ኛ ክፍል 96 ነጥብ 7 አማካይ ውጤት በማምጣት ከትምህርት ቤቱ ተሸላሚ እንደነበርም አስታውሷል። 

 የዶዶላ ኢፈ ቦሩ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዴቱ ዲቦ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ 125 ተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል ፈተና ማስፈተኑን አስታውሰዋል። 

ከተፈተኞቹ መካከል የትምህርት ቤቱ ተማሪ ካሊድ በሽር 591 በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። 

የተቀሩት ተማሪዎችም ከ482 በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የገለጹት ርዕሰ መምህሩ የተመዘገባው ውጤት በትምህርት ቤቱ መምህራንና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ደስታና መነቃቃት መፍጠሩን ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም