የ2018 የትምህርት ዘመንን በስኬት ማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የ2018 የትምህርት ዘመንን በስኬት ማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በስኬት ማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።
የትምህርት ዘመኑን በውጤታማነት ማጠናቀቅ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ሚኒሊክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በመገኘት የትምህርት አጀማመርን ተመልክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነት እና ተገቢነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሪፎርሞች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
በመምህራን አቅም ግንባታ፣ በቅድመ አንደኛ ትምህርት እና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ረገድ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ስራዎች የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በቂ እውቀት እና ክህሎት በመያዝ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ እና የተሻለ የመማር ማስተማር እንዲኖር ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል የወላጆች እና የመምህራን ሚና የማይተካ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎችም ለትምህርታቸው በቂ ጊዜ በመስጠት በፕሮግራም መመራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
መምህራንም በትምህርት ላይ ያለውን ውጤታማነት ለማሳደግ እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ተማሪዎቹም በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።