ቀጥታ፡

 የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እና የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትና የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማሻሻል እንዲሁም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በ2018 ዓ.ም ትምህርት መጀመርና የአደባባይ በዓላት ጋር ተያይዞ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የማስፈፀሚያ እቅድ አቅርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ ያብባል አዲስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትና የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማሻሻልና የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በተለይም በ2017 በጀት ዓመት ተግባራዊ በተደረገው የሪፎርም ስራ በመዲናዋ የትራፊክ ፍሰት እና የመንገድ ደህንነት ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልፀዋል።

የመስከረም ወር ትምህርት ቤት የሚከፈትበትና በርከት ያሉ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት፣ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ቁጥር የሚጨምርበት እና የትራፊክ መጨናነቅ የሚከሰትበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባትም ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል እቅድ በመንደፍ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት ለመንገድና ለትራንስፖርት ልማት የሰጠው ትኩረት ለትራፊክ ፍሰት መሻሻልና አደጋን ለመቀነስ አይነተኛ ሚና ማበርከቱን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ መስከረም ትምህርት የሚከፈትበትና የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት በመሆኑ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና እንዳያሳድር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።


 

በዚህም ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች በመለየት በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጥሩ ከመንገዶች ባለስልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥገና ለማከናወን በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አካሉ አሰፋ በበኩላቸው በዚህም ከ200 በላይ አውቶብሶች ላይ ጥገና በማድረግ ወደ ስምሪት እንዲገቡ መደረጉን ገልፀው የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


 

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ሃላፊ ኢንስፔክተር ያደሳ ቸኮል በበኩላቸው ከትራንስፖርት ፍሰትና ከትራፊክ ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ አካላት በቅንጅት መስራት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም