በሲዳማ ክልል ከተሞችን በማዘመን ለኑሮ ምቹ እና የጉብኝት ማእከል እንዲሆኑ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ከተሞችን በማዘመን ለኑሮ ምቹ እና የጉብኝት ማእከል እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ የክልሉን ከተሞች የማንሰራራት ጉዞ ለማፋጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ተናገሩ።
የሲዳማ ክልል መንግስት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ዓመታዊውን የሴክተሮች ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ አካሄዷል።
በጉባኤው ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፤ በሲዳማ ክልል ከተሞችን የማዘመን፣ ለኑሮ ምቹና የጉብኝት ማእከል እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የከተሞች ልማት አዳዲስና ዘመናዊ አሰራሮችን ተከትሎ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የክልሉን ከተሞች ፅዱ፣ ውብና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቀጣይ የኮሪደር ልማት ስራዎችን የማስቀጠልና የከተሞችን ውበት የማስጠበቅ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የዲጂታል አሰራርን የተከተሉ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሩ፤ የክልሉን ከተሞች እድገት ለማስቀጠል የከተማ ልማት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በፕላን እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተሞች ጥራታቸውን የጠበቁ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን የማስፋት፣ የኮሪደር ልማትን የማስቀጠልና የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር መሰረተ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ኢንጂነር ምህረቱ ገብሬ፤ በከተማዋ የመጀመሪያውን ምእራፍ ሁለተኛ ክፍል የኮሪደር ልማት በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የ5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ፣ ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛና የብስክሌት መንገድን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፓኬጆች ያሉት መሆኑንም አንስተዋል።