ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን  ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

 ባሕር ዳር ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን  ለመፍታት  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።  

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ እና የመሬት ቢሮ  አመራሮችና ሰራተኞች የሕዳሴው ግድብ ምረቃን ምክንያት በማድረግ በባሕርዳር ከተማ ዛሬ  ተወያይተዋል።  

የሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ  ብርቱካን ሲሳይ  በወቅቱ እንዳመለከቱት፤  ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን  እናቶች  በቦንድ ግዥና በድጋፍ አስተዋጽኦ አድርገዋል።


 

ይሕም የበለጸገችና ለሌሎች የምትተርፍ ሀገር ለልጆቻቸው ለማስረከብ ያላቸውን ቁጭት ለመወጣት በማለም መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋት እናቶችን  ማገዶ ፍለጋ ከመንከራተት የሚያስቀር ከመሆኑም ባሻገር  ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ተጠቃሚ  እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

የግድቡ ግንባታ መሳካት የገጠሩን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድረግ የሴቶችን ጫና የሚያቃልል ነው  ያሉት ደግሞ በቢሮው የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር  ወይዘሮ ካሳየ ያለው ናቸው።

በተለይም ሴቶች ኤሌክትሪክን ተጠቅመው በሚሰሩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመሰማራት ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በቢሮው የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር  ወይዘሮ ፈለቀች ፈንቴ ፤ ግድቡ ተጠናቆ መመረቅ መቻሉ በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑ አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ የበርካታ እናቶችን የኑሮ ዘይቤን እንደሚቀይር ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የክልሉ  መሬት ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች  ‎"የሕዳሴ ግድብ፤ የብልፅግናችን አሻራ" በሚል መሪ ሃሳብ በተወያዩበት ወቅት ‎‎‎የቢሮው  ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ፤ የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ አይችሉም የሚለውን ችለን ለዓለም ሕዝብ ያሳየንበት አኩሪ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። 


 

‎ለግድቡ ግንባታ ሕዝቡ  ካደረገው ድጋፍ ጎን ለጎንም ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በችግኝ ተከላና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አብራርተዋል። 

‎‎በዕለቱም የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች ለ50 ተማሪዎች የደብተር፤ የቦርሳና የእስክሪብቶ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም